News (ዜና)


የጤና ቡድኑ አባላት ‘የፍቅር መዓድ’ ዝግጅትን አከበሩ

መጪውን የአብይ ጾም መያዣ ምክንያት በማድረግ ‘የፍቅር መዓድ’ የተሰኘ ዝግጅት በቅ/ገብርኤል ት/ቤት ቅጽር ግቢ ውስጥ አብዛኛው የጤና ቡድኑ አባላት በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከበረ፡፡ የዝግጅቱ አስተባባሪና የቡድኑ ኮሚቴ ጸሐፊ የሆኑት አቶ ደረሰ ጫላ የዚህ ዓይነት ፕሮግራም መዘጋጀቱ ለቡድኑ የሚኖረውን ፋይዳ አስመልቶ ሲናገሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ የታሰበ የጋራ የጾም መያዣ ፕሮግራም መሆኑና በተለይ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲን ለመደገፍ በሚደረገው የሰልፍ ዋዜማ ላይ ፕግራሙ መዘጋጀቱ ልዩ እንደሚያደርገው  የገለፁት የቡድኑ ጸሐፊ በአባላት መካከል የሚኖረውን መልካም መንፈስ ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አክለው ተናግረዋል::

በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን የቅ/ገብርኤል ት/ቤት ዳይሬክተርና የጤና ቡድኑ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ ኃይለኛው በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የጤና ቡድኑ መቋቋም ለት/ቤቱ መምህራን የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ለወደፊት ጤና ቡድኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ት/ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በዝግጅቱ ማጠቃለያም ለጤና ቡድኑ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የቀድሞ የኮሚቴ አባላት የዕውቅና የምስክር ወረቀት የመስጠት እና ለት/ቤቱ የጥበቃ አባላትም የገንዘብ ሽልማት በማበርከት ዝግጅቱ ተጠናቅቋል፡፡

የካቲት 12 2012 ዓ.ም


ሦስት የቡድን አባላት ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ተወሰደ

የቡድኑ አባል የሆኑት ብርሃነመስቀል ዳዊት እና አንዱዓለም ይልማ በልምምድ ሜዳ ላይ ባሳዩት ስነ-ምግባር የጎደለው ያልተገባ  ድርጊት ምክንያት ኮሚቴው የዲሲፕሊን እርምጃ ወስዶባቸዋል፡፡ በመሆኑም ብርሃነመስቀል ዳዊት የ 3 ጨዋታ እና የ 2 መቶ ብር ቅጣት ሲተላለፍበት አንዱዓለም ይልማ ደግሞ ለ 1 ወር ከማንኛውም ጨዋታ እንዲታገድ እና 500 ብር እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

በተያያዘ ዜና የቡድኑ አባል የሆነው ሰለሞን ደመና ባሳየው ያለተገባ የሜዳ ውስጥ ተግባር የ 3 ጨዋታና የመቶ ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡

ጥር 19 2012 ዓ.ም


ገብርኤሎቹ ከ ሚሚ ሱ/ማ ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ አደረጉ

ገብኤሎቹ ከ ሚሚ ሱፐር ማርኬት ጋር ባደረጉት ጨዋታ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ የድል ግቦቹንም የመሀል ተጫዋች የሆነው አሸናፊ አብሃም ጨዋታው በተጀመረ በ 6ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ጎል በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል:: ሁለተኛውን ጎል ደግሞ ከዳግም ደግፌ የተሻገረለትን ኳስ ሰለሞን ግዛው በ 13ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር፤ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የፊት መስመር አጥቂ የሆነው ዳግም ደግፌ ሰለሞን ያስቆጠራትን ግብ አመቻችቶ ከማቀበሉም በተጨማሪ በ 27ኛው ደቂቃ ሦስተኛውን ጎል በማከል ቡድኑ በ 3 ጎል ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል፡፡ ሚሚዎቹ ከእረፍት በፊትና ከእረፍት በኃላ አንድ አንድ ጎል በማስቆጠር ውጤቱን ለመቀየር ቢጥሩም የኃላው መስመር ላይ ደጀን ሆነው በዋሉት ተከላካዮቹ አንበርብር ፊሊጶስ እና ሰለሞን ደመና ድንቅ ችሎታ ታግዘው ገብርኤሎቹ ጨዋታውን 3 2 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል፡፡  

ጥር 10 2012 ዓ.ም


ቡድን ሀ እና ቡድን ለ የወዳጅነት ግጥሚያ አደረጉ

ቡድን ሀ እና ቡድን ለ የተዋቀሩት ከ ቅ/ገብርኤል ጤና ስፖርት ቡድን አጠቃላይ አባል ከሆኑ 40 አባላት ውስጥ ለ ሁለት በተከፈሉ 19 – 19 የቡድኑ አባላት ሲሆን በተደረጉት ሁለት የእርስ በእርስ የወዳጅነት ግጥሚያዎች ላይ የመጀመሪያውን ታኅሳስ 4 2012 ዓ.ም ሁለት ለ ሁለት በሆነ አቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሁለተኛውን ጨዋታ ደግሞ ታኅሳስ 15 2012 ዓ.ም ቡድን ለ ( 2 – 0 ) ሁለት ለ ባዶ በሆነ ውጤት ሊያሸንፍ ችሏል፡፡ የቡድን ለ አባላትም በተገኘው ድል መደሰታቸውን ገልጸው ወደፊት የተሻለ  ነገር ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ሲናገሩ፤ በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ የኳስ ፍሰት ያለው እንቅስቃሴ ማሳየት የቻሉት የቡድን ሀ አባላት ደግሞ እንደ አጠቃላይ ልምድ ያገኙበት ጨዋታ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ግን በሁለተኛው ጨዋታ በተገኘው ውጤት ማዘናቸውን ገልጸው ጫወታው ፍታዊ እንዳልነበረና ተቃራኒው ቡድን ኃይል የተቀላቀለበት የአጨዋወት ዘዴን በመምረጡ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸው በማከል ወደፊት ግን የተሻለ  ነገር ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

 ታኅሳስ 15 2012 ዓ.ም

Design a site like this with WordPress.com
Get started